T
Tsegaw Mamo
3 reviews ·
0 followers ·
September 17, 2026
5/5
"ድርሰት የሌለው ሕዝብ ሕዝብ አይደለም" (ቮልቴር)
የሀገርና የሕዝብ ጉዳይ እረፍት ከሚነሳቸው ዋነኞች አንዱ ከበደ ሚካኤል ናቸው። የኢትዮጵያ ኋላቀርነትና ድንቁርና በአያሌው አሳስቧቸዋል ። ስለ ሥልጣኔ ከጻፉት አራት መጻሕፍት አንዱ ይኸ ነው።
--------------
"ደራሲ የሌለው ሕዝብና ቃፊር የሌለው ወታደር አንድ ነው " ሁለቱም መሸነፋቸው አይቀርም ይላሉ አስረስ የኔሰው ። የአንድ ሕዝብ እድገት እና ሥልጣኔ የሚታወቀው ኪነ -ጥበቡም ሲያድግ ነው ። "Art is the signature of civilizations." እንዲል Beverly Sills ። የጥሩ ድርሰት ማደግ የሕዝብን ማደግን ያመለክታል ። ከበደ ሚካኤል ግሪክ ሚጢጢዬ ሀገር ሆና ሳለ ኃያላን ሃገራትን ሳይቀር በትንሽ ጦር ያንበረከከችው ሥልጣኔ ስላላት ነው ይላሉ። ሥልጣኔ ያለው ሕዝብ ከነጻነቱ ባሻገር በአሸናፊነት ይኖራል። ኋላቀርነት የባርነትና የድህነት ምንጭ ነው።
---------
ከበደ ሚካኤልም የግሪክ ሥነ ጽሁፍ ትሩፋትን በሆሜር በኩል እንዲህ ይገልጡታል።
"ዓለም በድንቁርና ተንኮል ሲኖር ብቻዋን በሥልጣኔ ጸድቃ ትኖር የነበረችው ግሪክ ውበቷን የሚመሰክሩ ሕንጻዎቿ ዛሬ ፈርሰዋል ፣ አርበኞቿም ረግፈዋል የሆሜር ቅኔ ግን እስካሁን ድረስ ቆይቶ ግሪክ ምን እንደነበረች ይገልጣል ያስተምራል ፤ ይናገራል"
ገጽ 24 "በማንኛውም ሕዝብና በማናቸውም አገር በማናቸውም ዘመን ከተነሱት ባለቅኔዎች ሁሉ ሆሜር ይበልጣል ከዚህም የተነሳ የባለቅኔዎች መሥፍን ተብሎ ይጠራል" ... ረናን የሚባለው የፈረንሳይ ሊቅ ከአንድ ሺ ዓመት ወደፊት እውቀት እየሰፋ ሲሄድ ... አሁን በዓለም ላይ ያሉ መጻሕፍት ሁሉ ተንቀው የሚያነባቸው ይጠፋል ። ሁለት መጻሕፍት ብቻ ምንጊዜም ቢሆን ስለማይረክሱ መታተማቸውና መነበባቸው ይቀጥላል እነዚሁም መጽሐፍ ቅዱስና የሆሜር ቅኔ ናቸው"ገጽ 27 ። የሆሜር ድርሰት ለ3,000 ዘመን አዲስ ሆኖ ሊቀጥል የቻለው ምን አይነት ድርሰት ቢሆን ነው ? ለምን ወደ እኛ ቋንቋ ተተርጉሞ አላነበብነውም ? ግሪኮች የፈነጠቁት የእውቀት የብርሃን ጮራ ዛሬም በብዙ የምድራችን ሥፍራዎች ያበራሉ። ትልቁ ጥያቄ ለምን በእኛ ሀገር አላበሩም ?የሚለው ነው ።
------------------
"ሰው ባሳቡ ካልተመራመረ በቀር ሕይዎት አለኝ ለማለት አይገባውም " ይላሉ። ይቀጥሉና
"ሕዝብ በእንቁላል ሊመሰል ይችላል። እንቁላል ካላስታቀፉት በስተቀር አይፈለፈልም ፣ ሕይዎትም አያገኝም። ሕዝብም እንደዚሁ በእውቀት ካልቀሰቀሱት በቀር ዓይን አይከፍትም እንደ እንቁላል ተደፍኖ ይኖራል እንጅ ይህም ተደፍኖ የሚኖርበት ሁኔታ የአእምሮ ሰመመን፣ የመንፈስ እንቅልፍ ድንቁርና ይባላል" ይላሉ ።ሕዝብ በድርሰትና በኪነ ጥበብ ካልተቀሰቀሰ በጽኑ የእንቅልፍ ድንዛዜ ውስጥ እንደሚኖር የዕውኑን ዓለም ምሥክርነት ከግሪክ እየጠቀሱ ይነግሩናል ። ማሰብ አንችልም ደንቆሮ ነን ስለዚህ ሕይዎትን እየኖርናት አይደለም የሚሉ ይመስላል ።በዚህ ጉዳይስ ላይ መቼ ተነጋገርን ?
---------------
ከበደ ሚካኤል በዚህ መጽሐፍ ላይ ስለ ባርነትና ነጻነት ፣ ስለ ኪነ ጥበብና ሥልጣኔ ፣ ስለ ኪነ ጥበብ ሰዎችና ሳይንቲስቶች ለጥበብና ሳይንስ ሁሉን ትተው እንዴት እንደ መነኑ በሚያስደንቅ ሁኔታ ይተርኩልናል። ክቡር ከበደ ሚካኤል ሆይ ስለ ብርቱ ጥረቶትና ቁጭቶት ምሥጋና ይገባዎታል!
በጸጋው ማሞ
